አማራ አልተወከለም - ከኢትዮጵያዊው

ባለፈው እሁድ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች (አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ፣ የሲዳማ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ተጣምረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄን መስርተዋል።

“የአማራ ሕዝብም አልተወከለም ስለዚህ ጥምረቱ ሙሉ እንዲሆን የአማራን ሕዝብ የሚወክል ፓርቲ ፈልጉ” ሲባል ሰምቼ አዘንኩ። ከጎደለስ የአማራ ብሄር ብቻ ነው እዚህ ጥምርት ውስጥ የጎደለው? መቶም አባል ይኑርው ሁሉም ብሄር ተወካዮን ማየት ይፈልጋል።

እውነት ይህ አካሄድ በሀገራችን ለተንሰራፋው መጠነ ብዙ ችግር መፍትሄ ነውን?

እኔ እስከሚገባኝ የብሄር ፖለቲካ፤ አቅም ሳይኖራቸው ብሄሬ አልተወከለም በሚል ጠባብ ፖለቲካ ድጋፍን አሰባስበው ስልጣን ላይ ለመወጣት ከሚደረግ ሩጫ በስትቅር እንወክልህ ለሚሉት ህዝብ ጠብ የሚል ነገር እንደማይኖር እሙን ነው።

ለማሳያነትም ዳግማዊ ዐፄ አምኒሊክም ሆኑ ሕ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ ሲነገሱ ሙሉ የአማራ ህዝብ ጠግቦ አላደርም፣ ደልቶትም አልኖረም እንደተቀርው ህዝብ በአስትዳደሩ የሚደርሱ መከራዎችን ከቀሪው ሕዝብ እኩል ሲካፈል ነው የኖረው።

በኢህአዴግም (መለስ) መንግስትም መላው የትግራይ ህዝብ ጠግቦ አላደርም፣ ደልቶትም አልኖረም እንደተቀርው ህዝብ በአስትዳደሩ የሚደርሱ መከራዎችን ከቀሪው ሕዝብ እኩል ሲካፈል ነው የኖረው። እርግጥ ነው የየስርዐቶቹ  ሹማምንት እና ቤትሰቦቻቸው ግን በሁሉም ረገድ በልፅገውበታል።

የሚቀጥለው የስልጣን ባለቤትስ የራሱን ብሄር ሕዝብ ቁጭ አድርጎ ይቀልባልን? በፍፁም!!! በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ግን እራሱን፣ ቤተሰቡን እንዲሁም ዘመዶቹን ያንደላቅቃል እንጂ ለመላው ብሄሩ ለይቶ ምንም አያደርግም። የብሄር ፖለቲካን ለስልጣን መወጣጫነት ይጠቀማታል እንጂ።

በሌላም እይታ የየትኛውም ብሄር ስልጣን ሲይዝ መላውን የእርሱ ብሄር የሆኑትን ግብር እና ታክስ አልማርም፤ እናቶችም በጀርባችው እንስራ ተሸክመው ወንዝ መውርድ አልቀረላቸውም። ገበሬውም ከከብት እረሻ ወደ ትራክተር አላደገም። ስለዚህ ይህቺ የዘር ፖለቲካ ከፖለቲከኛው ውጪ ቀሪውን ህዝብ አትውክልም እና ትቅርብን።

እንደ ሌላው አለም የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሰርት ኢኮኖሚን፣ ዲሞክራሲን፣ ሃገራዊ ህልምን ወዘተ የሚያሳዩ አጀንዳዎች በመያዝ በነዚህም ጉዳዮች ላይ የሚግባቡ ግለሰቦችን በማሰባሰብ እንጂ ብሄርህ እገሌ ስለሆን በሚል ፈሊጥ የማልቀበለው አላማ ካላቸው ስብስብ ጋር መቀየጥን አልደግፈወም።

ወገኖቼ እፊታችን የተደቀነውን ችግር ለማለፍ የይድረስ ይድረስ የሚሰጥ መፍትሄ ዘለቄታዊ ችግር ፈቺ ባለመሆኑ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ለሚደረጉ ውሳኔዎች የሚሰጠውን ድጋፍ ሊያጤነው ይገባል ባይ ነኝ። “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል” እንዲሉ

አሁንም ብሄሬን ይውክል ብለን የምንልከው ግለሰብ ወይም ፓርቲ ከራሱ ላለፈ ነገር መስራቱን በምንም መልኩ እርግጠኛ እንሆንም።

እግዚዓብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!

ኢትዮጵያዊው

11/05/2016