አገር በቀላሉ የሚሰባብሩት ሸክላ አይደለም [ አገሬ አዲስ]

አገር ትውልድ በደምና ባጥንቱ ገንብቶ ለተተኪው ትውልድ አስረክቦ የሚያሳልፈው ቅርስ ነው፤ተተኪውም ትውልድ የተሰጠውን አደራ ጠብቆ ለሱ ተተኪ አሳልፎ የሚሰጠው ቋሚ ገጸበረከት ነው።አገር የአንድ ሕዝብ ማንነትና ምንነት መግለጫ ፣መታፈሪያና መከበሪያ፣ጥላና መከለያ፣መኖሪያና  ምሽግ ሲሞትም የሚያርፍበት የዘላለም ቤቱ ነው።የሰው ልጅ ካለአገር ሊኖር አይችልም፤አገር ማለት የዓለም አካል የሆነ በሰዎች አኗኗር የተከለለ መሬት ማለት ነው።የሰው ልጅ በአጋጣሚ የተፈጠረበት(የተወለደበትን) ወይም ተፈጥሮ አስገድዶት ከቦታ ቦታ እተዘዋወረ በመጨረሻው   የሚሰፍርበትን መሬት አገሬ ብሎ ይኖራል።አገር እንደ ሕዝቡ ብዛትና ሰፈራ፣የእድገትና አደረጃጀት ቅርጽ ይዞ የመሄድ ሂደትን ይከተላል።ከሰፈር ወደ ወረዳ፣ከወረዳ ወደ አውራጃ ከአውራጃ ወደ ክፍለሃገር ከዚያም ወደ አገርነት ደረጃ ለመድረስ ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ የሕይወትና የንብረት ዋጋ የሚያስከፍል ሂደት ነው።ከዚያ ውጭ በተፈጥሮ ይህ ለዚህ ሕዝብ  ብቻ ተብሎ የተቀመጠና የተወሰነ አይደለም። አገርን እንደ አገር ለመመስረት የተለያዩ መንገዶች ሲኖሩ በጆግራፊ አቀማመጥ የሚቀራረቡ ሰዎች በሚኖራቸው ግንኙነትና መቀራረብ ፣በቋንቋ፣በባህል፣የእርስ በርስ መስተጋብር ከባቢያቸውን የጋራ ንብረታቸው አድርገው አንድ አገር ይመሰርታሉ።በሌላም መንገድ ደግሞ በወረራና በፍልሰት አገር ይመሰረታል። አሜሪካ፣ አውስተራሊያ፣ ካናዳና እስራኤል ለዚህ ምሳሌዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ አገራችን ከዚህ ከሁለቱ አገር አመሰራረቶች ውጭ አልተመሰረተችም።የመጀመሪያውን ሂደት በመጠቀም በቀድሞ ዘመን የኖረው በልዩ ልዩ ማህበራዊ ግንኙነቶች የተቀራረበው ህዝብ በአንድ አገር ዜግነት እንዲኖር ጊዜው የሚጠይቀውን መንገድ  በሰላምና በጉልበት ተጠቅሞ የእኛ ትውልድ የተረከብናትን አገር ለመገንባት ችሏል።በዚህ አገር ግንባታ በሰላም ወደውና ፈቅደው፣የአንድነት ጥቅሙን ተረድተው የተቀበሉ እንዳሉ ሁሉ የዛም ተጻራሪ የሆኑት እንደነበሩና በሁለቱም መካከል ሊወገድ ያልቻለ ግጭትና ጦርነት እንደተካሄደ የማይካድ ነው።ይህ በእኛ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም አገሮች የተከናወነ የአገር ግንባታ ተመሳሳይ ሂደት ነው።የጥንቷ ግሪክ፣ ቻይና፣የአውሮፓም አገሮች ብዙዎቹ፣አሜሪካንም ሳትቀር እንደ አገር ለመኖር የበቁት፣ በአንድነትና ጸረ አንድነት በሆኑት መካከል በተደረገ የሞት የሽረት ትግል በአንድነት ሃይሉ አሸናፊነት ነው።ኢትዮጵያም እንዲሁ በአንድነትና በጸረ አንድነት መካከል በተደረገ ፍልሚያና በተከፈለ የህይወት ዋጋ የተመሰረተችና የተገነባች አገር ነች።

አገር ከተመሰረተም በዃላ አንዱ አገር ሌላውን በመውረር ያጣውን ለማግኘትና ለመዝረፍ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ለማሳደር በወረራ ላይ እንደሚሰማራ በታሪክ ታይቷል።በዚህ የወረራና የመቀራመት ዘመቻ የተሰለፉት  አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገሮች ነበሩ።ይህም ተሳክቶላቸው አጎራባች አገሮችን ብቻ ሳይሆን ውቅያኖስ ተሻግረው ብዙ አገሮችን በመዳፋቸው ስር ለማድረግ ችለዋል።ኢትዮጵያንም የዚያው ሰለባ ለማድረግ ተከታታይ ሙከራ ከማድረግ አልቦዘኑም ነበር።በቆራጥ ዜጎቿ ህብረትና ትግል የወራሪ ቀንበር ሊሰበር ችሏል።ወራሪዎች ካልተሳካላቸውም የውስጥ ቀውስ በመፍጠር ሕዝቡን በማለያየት በቁጥጥራቸው ስር በማድረግ  አዳክመው ለመዝረፍና ለመቆጣጠር ያልሞከሩበት ጊዜ የለም።ለዚያም የሚገለገሉት አንዱና ቀላሉ መንገድ አገር በቀል የሆነውን ክፍል በስነልቦናውና በደካማ ጎኑ እየገቡ፣ለእሱ ተቆርቋሪና ሃሳቢ መስለው በመቅረብ ፣የገንዘብና የመሳሪያ ብሎም የፖለቲካ ድጋፍ እየሰጡ በራሱ አገርና በወገኑ ላይ እንዲያምጽ በመቀስቀስ ነው።ኢትዮጵያ አገራችንም ከዚህ አይነቱ ተደራራቢ ተንኮል ሰለባ ከመሆን አላመለጠችም።

ነጮች፣ቱርኮችና አረቦች በተለያየ ጊዜ  በወረራ ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካላቸው በመቅረቱ ከሃምሳ ዓመት ወዲህ  ደግሞ በባሰና በተቀናጀ መልኩ እምነትንና ቋንቋን ተገን በማድረግ አንዱን በሌላው ላይ እንዲነሳ ያላሰለሰ ሙከራ አድርገዋል፤አሁንም በማድረግ ላይ ናቸው።የዚህ ውጤት የሆኑት በተለያየ ጎሳ ስም ሲንቀሳቀሱ የነበሩና አሁንም ያሉት ሃይሎች ናቸው። የኤርትራ፣የትግራይ፣የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባሮች ቀደም ያሉት ሲሆኑ ከሃያ አምስት ዓመት ወዲህ ደግሞ፣የሲዳማ፣የኦጋዴን፣የአፋር፣የጋምቤላ፣….ወዘተ ነጻ አውጭ ነን ባዮች እንደ እንቁላል ተፈልፍለው በራሳቸው አገር ላይ፣በወገናቸው ላይ፣ የክተት አዋጅ አውጀው እላይ እታች እያሉ ይገኛሉ። ዓላማቸው በነጻነትና በእኩልነት ስም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሆኑትን ዓላማ ተግባራዊ ማድረግ ነው።ለዚያ ጉዞ የሚረዳው ሕዝቡን ያስተሳሰረውን ገመድ መበጠስ ነው።በአንድ ቋንቋ እንዳይናገር፣የአንድ አገር ምልክትና መታወቂያ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ቀዶ ጥሎ የየራሱ የሆነ የተዘበራረቀ ቀለም ያለው ባንዲራ እንዲሸከም ማድረግ፣ከብሔራዊ ማንነት የጎሳ ማንነትን ማጉላትና ማስተጋባት፣በግል መስተናገድ የሚኖርበትን መብትና እምነት የማህበረሰብ መታወቂያ አድርጎ ማሰለፍ ቀላሉ መንገድ ነው።

ከአርባ አምስት ዓመት ወዲህ በተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ሳቢያ በግርግር አገራችንን ለመቀራመት ጫካ የገቡት በዘር ፖለቲካ የተለከፉ ሃይሎች በውጭ ድጋፍና እርዳታ ተሳክቶላቸው የዛሬ ሃያአምስት ዓመት ሥልጣን ላይ በመቀመጥ አገራችንን ወደመበታተን የምትጓዝበትን ስልት በመከተል በሕገመንግሥት ደረጃ ደንግገው ተራ በተራ የመሸራረፍ ሥራ ከጀመሩ ቆይቷል።ኤርትራን የመጀመሪያ ሙከራ በማድረግ ሌሎቹም እንዲቀጥሉበት በር ከፍቷል።አሁን ያ ጉዞ አገሪቱን ከመበታተን ጠርዝ ላይ አድርሷታል። ያንንም አደጋ  አንዱ ኦነግ የተባለው የጥፋትና ጸረ አንድነት ቡድን  በቅርቡ በአደባባይ ወጥቶ በአዋጅ አረጋግጦታል። ህወሃት የተሰኘው የሥልጣኑ ብቸኛ ባለቤት የሆነው ቡድን ለእኩልነትና ለአገር አንድነት የሚጮኸውን ሕዝብ እየጨፈጨፈ፣እያሰረና እያሳደደ ባለበት በዚህ ወቅት የሱ አጋርና ቢጤ የሆነው በጥቅም ግጭት ከሥልጣን ኮርቻ የተወገደው ኦነግ የተባለ ቡድን የኦሮሞ ተወላጆች ከሌላው ወገናቸው ጋር ሆነው በደማቸው የገነቧትን አገራቸውን የማፈራረሱን ምኞትና ፍላጎት በአደባባይ በድፍረት ሲገልጸው ተደምጧል።ይህ ምኞት የአንድ ሰው ሃሳብ ነው ተብሎ ለማስተባበል ቢሞከርም የአንድ ግለሰብ ፍላጎት እንዳልሆነ ነጻነት ወይም ሞት ብለው፣ባንዲራ ሰፍተው በልዩ ልዩ መጠሪያና ስልት የተሰለፉትን ማዬት ምስክር ነው።የሌሎቹም ተመሳሳይ የጎሳ ቡድኖች ፍላጎትና ዓላማ ከዚያ የተለዬ አይደለም። በግርግር ያባትህ ቤት ሲቃጠል አብረህ ዝረፍ ብለው፣ሁኔታው ሲባባስ የድርሻቸውን ለመቦጫጨቅ ቋምጠው የተሰለፉ ናቸው።የነዚህ የጥቂቶች እራስ ጠሌ መሆን ሌላውን ብዙሃኑን ከኢትዮጵያዊነት አያርቀውም።እነሱ ኢትዮጵያን እናፈራርሳታለን፣እንበታትናታለን  ብለው ሲነሱ ከኢትዮጵያውያኑ የሚያገኙት መልስ ጣሊያኖችና ሌሎቹም ወራሪዎች ያገኙትን መልስ ይሆናል፤ የተባበረ የሕዝብ ቅጣት!

የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሩን የግዛት አንድነትና ነጻነት በምንም መልኩ ሊደራደርበት አይችልም።ዳር ድንበሯን ለማስከበር እንጂ አሳልፎ ለመስጠት የተነሳ ሕዝብ አይደለም።በአንድ ሕዝብ፣በአንድ አገርና በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ያምናል።እራሱን እንደ አንድ ሕዝብ ይቆጥራል እንጂ የተለያዬ ይመስል ሕዝቦች ብሎ አይጠራም።ማህበረሰብ እንጂ ብሔርና ብሔረሰብ በሚል አወዛጋቢ ቃል ህዝብ አይከፋፍልም።የተለያዩ ማህበረሰቦች እንዳሉና የነሱም መግለጫ የሆነ ቋንቋ፣ባህል እንዳላቸውና ማሳደግና መጠቀምም እንዳለባቸው ያምናል።የአንድ ብሔራዊ ቋንቋ መኖር ይበልጥ ለመቀራረብና ለመግባባት ብሎም ለእድገት የሚረዳ መሆኑን ይገነዘባል።ከመዳበሩና ከአገልግሎቱ አንጻር ተመልክቶ ይህ ቋንቋ ይጠቅመናል ብሎ የሚመርጠው ግን ሕዝቡ መሆኑን ይቀበላል። በእኔ ግንዛቤ ግን ከጥቅምና አገልግሎቱ፣ ከቋንቋው ጥልቀት፣ካለው እራሱን የቻለ አገር በቀል ፊደላት፣የስነጽሁፍ ድርሻና ከተናጋሪው ብዛት አንጻር አማርኛ ቋንቋን መጠቀሙ ይበልጥ ልንኮራበት የሚገባ ነው እላለሁ።ቋንቋ ማንንም ሊጎዳ የሚችል ሳይሆን ለመግባቢያ የሚያገለግል አንዱና ዋና መሳሪያ ነው።አማርኛን መናገር ማለትም ሌላውን አማራ ያልሆነውን ኢትዮጵያዊ አማራ ማድረግ አይደለም። በዓለም ዙሪያ እንግሊዝኛ ተናጋሪ እንግሊዛዊ  እንደዳልሆነ ሁሉ!።ከሌላው ጋር የሚግባባበትን ቋንቋ እየተናገረ ከቤተሰቡና ከአካባቢው ተመሳሳይ ጎሳ ሕዝብ ጋር ግን በራሱ የጎሳ ቋንቋ ቢነጋገር መጥፎ አይደለም፤መብቱም ነው።አንድነቱንም አያናጋውም።እስከ አሁንስ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ ጎሳ ቋንቋ ሲነገር የኖረ አይደለምን?ያማ ባይሆን ኖሮ ቋንቋዎቹ ሁሉ አሁን ከደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ባልቻሉም ነበር። ከሃያአምስት ዓመት ወዲህ የተፈጠሩ ሳይሆኑ ለዘመናት ሳይታገዱና ሳይከለከሉ በሕዝቡ ሲነገሩ የቆዩ በመሆናቸው ነው። የተለዬ ቋንቋ መናገር የተለዬ አገር ዜጋ አያደርግም። ዋናው ነገር የቀና ልቦና ባለቤት መሆን ነው።እኔ በምኖርበት የአውሮፓ አገር ከመቶ ሃያ በላይ ቋንቋ የሚናገር፣በቀለሙና በእምነቱ የማይመሳሰል፣ ከተለያየ አገር የፈለሰ ሕዝብ ይኖራል፤የሚግባባበት ግን አንድ ያገሪቱ ቋንቋ ነው።የራሱን ቋንቋ ከሚናገሩት ጋር እየተነጋገረ በሰላም ይኖራል።የተለዬ  ቋንቋ ተናጋሪ ነህ ተብሎም ወደዳር አይገፋም ወይም ሰብአዊና የዜግነት መብቱን አይገፈፍም።

እኛ በአንድነት የምናምነው ኢትዮጵያውያን በዲሞክራሲና በመብት ስም ብሔራዊ ገጻችንን ለሚቀናቀንና ለሚያጠፋ ለውስጥም ሆነ ለውጭ ሃይል ማጎብደድ አይኖርብንም።የአገራችንን ፣ታሪክ፣ነጻነትና ክብር አስጠብቀን ለተተኪው ትውልድ ማስረከብ ግዴታችን ነው።ትግላችን የተሻለች ኢትዮጵያን በተሻለ ስርዓት ለመገንባት እንጂ ለመበታተን መሆን የለበትም።ከላይ እንደተገለጸው አገራት የተመሰረቱትና ነጻነታቸውን አስከብረው ለእድገት የበቁት ከጸረ አንድነትና ከወራሪ ሃይሎች የሚሰነዘረውን ጥቃት በመመከት እንደሆነ ሁሉ የአንድነት ሃይሉ አገራችንን ለማፈራረስ ከተሰለፉት ጋር ለመፋለም ዝግጁ መሆን ይኖርበታል።ስውር ተንኮልን ከቀና መንፈስ እያዩ መጃጃል ማክተም አለበት።ሻእቢያ የኢትዮጵያውያኑን ድጋፍ ለማግኘት ሲል የመጨረሻው ዓላማችን በአንድነት መኖር ነው፣ግን ሕዝቡን በነጻነት ስም ስለቀሰቀስነው አሁን ያንን ለመጠምዘዝ ያዳግታል፤ የእናንተን ድጋፍ አይቶ አቋሙን ሊለውጥና ወደ አንድነቱ አስተሳሰብ ሊመለስ ይችላልና ትግላችንን ደግፉ በማለት እንዳሳሳቱን በጊዜው ተገንዝቤአለሁ።አሁንም ተመሳሳይ ዘዴ እየተሰበከ ነው። እዛ ወጥመድ ውስጥ ዳግም ላለመግባት መጠንቀቅ አለብን።

አንድ ሰንደቅ ዓላማ የአብሮነት ምልክት ነው።ከዚያም በላይ የማንነትና፣የነጻነት አርማ ነው።የረጅም ዘመን ታሪክ ያለውንና ብዙ የህይወት ዋጋ የተከፈለበትን  አረንጓዴ ልምላሜና እድገት፣ቢጫው ብሩህ ተስፋና ነጻነት፣ቀዩ ፍቅርና መስዋዕትነት በሚል አገላለጽና ትርጉም፣በሶስት ደማቅ ቀለም የተዋቀረውን፣ሃይማኖትና ጎሳ የማይለየውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለሚቀጥለው ትውልድ አሳልፎ ለመስጠት መዘጋጀት አለብን።

አገር እንዲህ በቀላሉ በምኞት የሚፈርስ፣እንደ ሸክላም በቀላሉ ተከስክሶ የሚበታተን አይደለም።ብዙ ባለቤትና ጠባቂ አለው።የጋራ ቤቱን ፣አገሩን ለማፈራረስ የሚነሳ የቀወሰ ቡድን እንጂ  ጤነኛ ትውልድ አይደለም።አይኖርምም። አዲሱ ትውልድ እንኳንስ ያለውን አሳልፎ ሊሰጥ ቀርቶ የተወሰደበትንም ለማስመለስ የማይቦዝን ትውልድ ነው። ያም ቢሆን የጊዜ ጉዳይ ነው አይቀርም።

የአገርን አንድነት የሚሹ የፖለቲካ ድርጅቶች፣የሲቪክ ተቋማትና ግለሰቦች የተደቀነውን አደጋ ለመመከት በአንድ ላይ እንዲሰለፉ አሁንም ጥሪ  አቀርባለሁ።አገር ሳይኖር የፖለቲካ ስልጣን አይኖርም።በትግል ስም፣በሥልጣን ላይ ያለውን ቀበኛ ቡድን በመቃወም ስም፣የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል ስንኩል ግንዛቤ የየራሳቸው ባንዲራ ሰፍተው ልዩ ነን ብለው የሚንቀሳቀሱ የጎሳ ስብስቦችን አጠራቅሞ ለውጥ አመጣለሁ የሚል ቡድን ቢሳካለት ከአለው ስርዓት የተሻለ እንደማይሆን ሊታወቅ ይገባል።የጎሳ ፖለቲካ ንድፈ ሃሳብ ከጎሳ ጥቅምና ፍላጎት በላይ አልፎ አይሄድም።ስለሆነም ያለው ስርዓት በተመሳሳይ መልክ ቢተካ ያው በገሌ ነው።

አንድ ሕዝብ በዘረኛና ወገንተኛ በሆነ ስርዓት ያጣውን መብቱን ለማግኘት መነሳቱና መጠየቁ ተገቢና ትክክልም ነው።ግን የአገርን ህልውናና የሌላ ወገኑን ጥቅምና ደህንነት ከስርዓቱ ጋር አጣምሮና አያይዞ ለማሶገድና ለማጥፋት የሚደረገው እንቅስቃሴ ወደባሰ ችግር የሚያመራና፣ለሚታገሉትም ስርዓት ሆነ ለውጭ አገር ወራሪዎች የሚረዳ እንጂ ለተጨቆነ የአንድ አገር ሕዝብ መፈትሔ አያመጣም።በስርዓቱ የሚበደለው የስርዓቱ ባለቤት ያልሆነው ሁሉ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የስርዓቱ ባለቤት አይደለም፤ትግሉም የስርዓቱ ባለቤት ልሁን በማለት ነው።መፍትሔው ሁሉም በደለኛ በአንድ ላይ ተባብሮ የሚጨቁነውን ስርዓት አሶግዶ ሁሉንም በሚንከባከብ ስርዓት መተካት ብቻ ነው።ተገንጥሎ የሌላ አገር ዜጋ በመሆን አይደለም። የእራሱን  አካባቢ የማስተዳደር መብቱ ይከበርለት ሲባልም ከሌላው የሚነጠልበት ግንብ ገንብቶ ከዚህ ወዲህ የእኔ ከዚያ ወዲያ የአንተ ብሎ ይኑር ማለት አይደለም።ለተቀላጠፈ ሥራ፣ለእድገት፣የከባቢው ነዋሪ ሕዝብ የሚሳተፍበትና የሚቆጣጠረው አሰራር ይመስረት ማለት ነው። የአንድ አገር ሕዝብ  ቋንቋን ባማከለ ፌዴራሊዝም ይተዳደር ማለት ከትልቅ አገር በትንሽ መንደር፣ከራሱ ቤት ከባለቤትነት ወጥቶ ደባል ሆኖ ይኑር ማለት ነው።ያን አይነት አሰራር ደግሞ ሳያድጉና ሳይሻሻሉ ለእድሜ ይፍታህ ጭቅጭቅና ግጭት የሚዳርግ ነው።

ኢትዮጵያ በቆራጥ ልጆቿ መስዋእትነት ነጻነቷና አንድነቷ ተከብሮ ይኖራል!

አገሬ አዲስ