ግጥም በአፈ ሙዞች መሃል ....... (አሌክስ አብርሃም) August 21- 2016

አድንቁኝ ! ግዴላችሁም አድንቁኝ ! ጀግና ልበ ሙሉ መሳሪያ ተደቅኖብኝ እንኳን የማልፈራ ጓደኛችሁ ነኝ ......አድንቁኝ !!
.... አንድ ቀን በታሪክ ይች ፅሁፍ ታላቅነቷ ይወሳል ...አሌክስ ምናለ በሉኝ ቱ! አሁን ስፅፍላችሁ ሁለት ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከግራና ቀኘ ተደግኖብኛል .... በድምሩ አራት የእጅ ቦንቦች ሁለት ጩቤወችና ሁለት የተጠቀለሉ ገመዶችም አሉ ......አንድ መገናኛ ሬዲዮም አጠገቤ ተቀምጦ ‹‹እሽሽሽሽ ወይራ አስራ ስድስት ...ሽሽሽ ቀበሮ ..ሰባት.......ሽሽሽሽ ድመቱ ተይዟል ›› የሚሉና ሌሎችም ድምፆች ያሰማል .....
እኔ ወንድማችሁ
የሽ ሰው ግምት የመቶ ምሳ
አንድ ብቻውን ውሃ እሚያነሳ .......ዘራፍ ........እፅፋለሁ ይሄ ሁሉ ሳያስፈራኝ .....

አሌክስ ጀግናው ...አሌክስ ...ሳተናው ..አሌክስ .... እሳቱ .....አዎ አልፈራም ነገ ልጆቸ ‹‹አባባ እኮ ፊቱ ዌብ ካም ሳይሆን ጠመንጃ ተደግኖበት የሚፅፍ ጀግና ነበር ....›› ይላሉ (መቸም ‹የነገ ልጆች አይረቡም› ከሚል የትውልድ ትንበያ ጋር …ትውልድ ሜትሮሎጅ እንበለው ይሆን ሃሃ) …አንዳንድ የታሪክ ሙህራን ‹‹ አሌክስ ሲፅፍ አንዳንዴ ከሃሳቡ የሚያፈነግጠው ...በብዛትም ፊደሎችን ያለቦታቸው የሚሰነቅረው በአንድ አይኑ የኮምፒውተር ስክሪን በሌላኛዋ የተደገነበትን መሳሪያ እያየ ይፅፍ ስለነበረ እንጅ ቸልተኛ ሁኖ አይደለም ›› ይላሉ፡፡ የሆነ ሁኖ ‹‹አሌክስ አብርሃም ጀግና ነበር›› የሚለው ነጥብ ....መደምደሚያቸው እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም ....እናንተስ ?
ከመልሳችሁ በፊት እችን አንብቧት ..................

ኢንተርኔት ቤትን ያንቀጠቀጠ ትውልድ ..........

በመደዳው የተሰደሩት የኢንተርኔት ቤቱ ኮፒውተሮች ፊት... ጎን ለጎን የተቀመጥነውን የኢንተርኔት ተጠቃሚወች ላስተዋውቃችሁ.......
እዛጋ የመጀመሪያው ‹ፒሲ› ላይ ......ጥቁር ጎልማሳ ... በሰቀሰቀው ዩኒፎርሙ ምክንያት አስፈሪ ጠባሳ የተጋደመበት ክንዱ እኔ ካለሁበት እርቀት ቁልጭ ብሎ የሚታይ የፌዴራል ፖሊስ! (ስካይፒ እየተጠቀመ)

2ኛ . ጠይም ወጣት ...አልፎ አልፎ ፉጨት የቀላቀለ አሰቃቂ ሳል የሚያስል (ኡሁ ኡሂሂሂኡፉፉፉፉፉፊፊፊፊፊፊ ጭጭጭጭጭ) በጣም ወደስክሪኑ ተጠግቶ ሲመለከት የአይን አሻራ የሚሰጥ የሚመስል ፌዴራል ፖሊስ! (ስካይ ፒ እየተጠቀመ)

3ኛ. የመሳሪያውን አፈ ሙዝ ወደቁጥር አራት ተጠቃሚ አዙሮ ጉልበቱ ላይ ያስቀመጠ… ወገቡ ላይ ሁለት ቦንብ አንድ ጩቤ አንድ የተጠቀለለ ገመድ (መልክቱን በኢንተርኔት ሳይሆን በወንጭፍ ያደረስ ይመስል) የታጠቀ ፌዴራል ፖሊስ ...(ስካይ ፒ እየተጠቀመ)

4ኛ. እኔ......!!!!!!!!!!!!! እኔ አሌክስ አብርሃም ነብስና ስጋየ እየተሟገተ ....ወታደሩ ወንበሩ ላይ ለመመቻቸት በተንቀሳቀሰ ቁጥር በድንጋጤ እጆቸ ኪቦርዱን ስተው ጠረንጴዛውን እየጠቀጠቁ

5ኛ. መሳሪያውን ወደእኔ አዙሮ ጉልበቱ ላይ ያስቀመጠ ፌዴራል ፖሊስ .....ሁለት ቦንብ አንድ ጩቤ አንድ ገመድ እንደታጠቀ .........

6. ሴት ፌደራል ፖሊስ(ፖሊሲት) ሙሉ የፌዴራል ፖሊስ ልብስ የለበሰ ወታደር ጋር (በስካይ ፒ እያወራች ).......
......... .............በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሁኘ እየፃፍኩ መሆኑን በመ , ዳት (ይቅርታ በመረዳት) ለሚከሰቱ የቃላት ግድፈቶች ‹አፉ› ማለት አትርሱ!!

‹‹ይሄ ሁሉ ወታደር ያለበት ምን ልትሰራ ሄድክ›› የሚል ጥያቄ እንኳን እናንተ እኔም ለራሴ አነሳለሁ ....እንግዲህ ወደ ኢንተርኔት ቤቱ ስገባ ባዶ ነበር... አንዲት ኑሮ የሰለቻት የምትመስል ልጅ ብቻ አንዱ ፒሲ ላይ የድሮ ፎቶዋን እየመላለሰች በማየትና ኩርቱ ፌስታል የሚያህል ማስቲካ በማላመጥ ስራ ተጠምዳለች ...ገብቸ ቁጭ አልኩና ግጥም መፃፍ ጀመርኩ ....ለፌስ ቡክ ጓደኞቸ ክረምቱን ያማከለ ርእስ መርጨ ...ግጥሙን ጀመርኩት.....
አንዳንድ ሰወች በዚህ ክረምት ስለመለያየት እየፃፉ ወደፌስቡካችን ስንገባ ፈሪጅ ውስጥ የገባን እስኪመስለን..ድባቡን ማቀዝቀዛቸው ያስከፋኛል ለምሳሌ.....

ሰኔ ግም ሳይል ብትሄጅብኝ ጅዳ
ብርድልብሴ ሳሳ መንፈሴም ተጎዳ
በፌስ ቡክ አዋሪኝ ሮብ በማለዳ
ስራ ካልበዛብሽ የኔዋ ሰአዳ ..... እኛ በምነ እዳችን ነው በደይቃ ስሙኒ እየከፈልን ሙሾ የምናነበው ......ሌላኛው ደግሞ ዛሬ ወባየ ተነስቶ እያንዘፈዘፈኝ ስለሆነ ፀልዩልኝ …ብሎ እኛንም ያንዘፈዝፈናል …. በዚህ አጋጣሚ 81 81 ላይ የፆለት አገልግሎት ለመጀመር ሃሳብ አለኝ …. ለምሳሌ ጉንፋን የያዘው ሰው እንድንፀልይለት ከፈለገ 8181 ‹ጉ› ብሎ ይልካል … ወይም ፍቅረኛው የከዳችው ሰው እንዲፀለይለት ከፈለገ ‹‹ፍ› ብሎ ይልካል ‹ፍንገላ› ማለት ነው ! ወደዋናው ርእሴ ስመለስ እንዲህ ብርድና ትካዜ የሞላውን ፌስቡክ ሞቅ ለማድረግ ሞቅ ያለ ርእስ ነበር ለምፅፈው ግጥም የመረጥኩት..እንደሚከተለው ...

ወይ ገንፎ!! (እርእሱ ነው)

ቅቤና በርበሬው በውስጡ ተንሳፎ
አዳሜ ሊበላው በጣም ተንሰፍስፎ ....እያልኩ አንድ ሁለት ፔጅ እንደፃፍኩ.....

‹‹ አይመጣም ብለሽ ነው ... ሌላ ወንድ የደረብሽብኝ ?...ሱዳን ዳርፉር እኮ ቅርብ ነው ..... ቆይ ጠብቂኝ ....መጥቸ አይንሽን ባላጠፋው እኔ ዘነበ አሰፋ አይደለሁም የጀግናው ቀይ ቆብ ለባሽ ሳንጃው ክፍለ ጦር አባል አይደለሁም ቱ ! ›› የሚል ድምፅ ሰማሁና ደንግጨ ዞር ብል አንዱ ፒሲ ላይ ፌዴራል ፖሊስ ተቀምጦ (መቸ ገብቶ ነው) በስካይ ፒ ሱዳን ዳርፉር ያለች ወዳጁ ላይ ይዝታል ...ቱ ሲል እንደጋለ ብረት ምጣድ የኮምፒውተር እስክሪኑ ችስስስ አለ ! (ሃሃ) ድንጋጤው መለስ ሲልልኝ ግጥሜን ቀጠልኩ ‹‹ምን እዚህ ጥበብ ያደናቅፋሉ›› ብየ በሆዴ ከተነጫነጭኩ በኋላ !!

‹‹ገንፎየ ገንፍሻ የብርድ ማስታገሻ ....›› የሚለው ላይ ስደርስ ደግሞ ... ሁለት ሙሉ ትጥቅ የታጠቁ ፌዴራል ፖሊሶች ኮስተር ብለው ወደውስጥ ገቡና ከግራና ቀኘ ተቀመጡ ....ከበቡኝ ! .....አይምሮየ ባንዴ ሚሊየን ነገር ያምሰለስል ጀመር ....ምን አጠፋሁ ....

‹‹ ስለገንፎ መፃፍ ሽብር ይሆን እንዴ .....
‹‹ ሳልሰማ ገንፎም ፖለቲካ ሁኖ ይሆን .... ወይስ ገንፎ ነክ ስም ያለው ህገ መንግስቱን በጉልበት ለመናድ የሚሞክር ተቀዋሚ ፓርቲ ይኖር ይሆን ?
....ለምሳሌ ‹‹ ኢገበዲፓ የሚባል(......የኢትዮጲያ ገንፎ በቅቤ ለዲሞክራሲ ፓርቲ ››) ...ማን ያውቃል ...ገንፎን እንደሽፋን በመጠቀም ፖለቲካዊ ትርፍ ለማጋበስ የሚሞክሩ ፀረ ሰላም ሃይሎች ሊኖሩ ይችላሉ! .....ይሄ ... ፓርቲ ምርጫ ቀረብ ሲል በቴሌቪዥን እንዲህ አይነት ቅስቀሳ ሊያደርግ ይችላል ...ስል አሰብኩ ....

‹‹ጭቁኑ የኢትዮጲያ ህዝብ ጥያቄው የገንፎ ነው ስንል ....ገዡ መንግስት " ገንፎውን ለሁሉም ኢትዮጲያዊ በእኩልነት ነው ያቀረብኩት" ይላል .......በዚህ እኛም እንስማማለን !! ...ልዩነታችን ማንኪያው ላይ ነው!! መንግስት ለህዝቡ የሻይ ማንኪያ ሰጥቶ ...በሾርባ ማንኪያ ገንፎ የቆነጠሩትን....ሙሰኛ ይላል ... ህዝብ አለቀ አላለቀ እያለ በስስት ...በሻይ ማንኪያ የሚቀምሳትን ገንፎ የራሱ ሰወች በጭልፋ ሲሞለቅቁት... እንኳን "ተው" ሊል ጭራሽ ቅቤ ማጥቀስ እንዳይረሱ ያስታውሳቸዋል!! !! ስለዚህ እኛ ብንመረጥ ለሁሉም የኢትዮጲያ ህዝቦች ብሄሮች ብሄረሰቦች .....ገንፎ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን እኩል መጠን ያላቸውን ማንኪያወቸንም እናድላለን ..................››

በሃሳብ ስባዝን ሁለቱም ፌዴራል ፖሊሶች ጆሯቸው ላይ ማዳመጫውን አደረጉና በስካይ ፒ ያወጉ ጀመር .....እፎይ!
ከዛ በኋላ ግን ግጥሙን መፃፍ አልቻልቻልኩም ... የምጠቀማቸው ቃላት ሁሉ ፖለቲካዊ ትርጉም ያላቸው እየመሰለኝ እደነብር ጀመር ...

ገንፎው ባንድ በኩል በጣት ሲቆነጠር
ቅቢያችን እንዳይፈስ ወደሌላ ድንበር .....
...........በግራ በኩል የተቀመጠው ወታደር ድንገት ወደኔ ዞሮ አንገቱን ሲያሰል ‹‹ሲቆነጠር›› እና ‹‹ድንበር›› የሚሉትን ቃላት አጠፋሁ.....እሱ ግን ባለ ኢንተርኔት ቤቷን በምልክት ኔትወርኩ እንደተቋረጠበት ነግሯት አንገቱን ወደቦታው መለሰ...ተመስገን !!

ቀጠልኩ ግጥሙን .......
ገንፎው ባንድ በኩል የተቆነጠረው
አብሮን የቀረበው ቆንጣሪ ቢሆን ነው ....
በቀኘ በኩል ያለው ፌዴራል ኮስተር ብሎ ዞር ሲል ፈራሁና ‹‹ቆንጣሪን›› አጥፍቸ መፃፌን ቀጠልኩ ........

የሰሃኑን ገንፎ እየቆነጠሩ
የአገር ሰሃኖች ባዷቸውን ቀሩ ...የሚያስለው ፌዴራል ፖሊስ አሳለው .... አሳሳሉ ከወትሮው ለየት ያለ ስለነበር ፈራሁ ..‹‹ አገር›› እና ‹‹ባዶ›› የሚሉትን ደንግጨ አጠፋሁ ........
ምን እንደምፅፍ እያሰብኩ እንዳለ ከጎኔ የተቀመጠው ወታደር ጉልበቱ ላይ ያስቀመጠው ክላሽ ላይ አይኔ አረፈ ..አፈሙዙ በትክክል የግራ ኩላሊቴ ላይ ነበር የተነጣጠረው ....ወደቀኘ ስዞር በቀኝ በኩል ያለው ክላሽ የቀኝ ኩላሊቴ ላይ ....ይሄ ነገር አጋጣሚ አልመስልህ አለኝ ...አንዱ መሳሪያ ቢባርቅ ወይም ባረቀ ብለው ቃታውን ቢስቡት ....ሁለቱን ኩላሊቶቸን በስቶ ሌላኛው መሳሪያ አፈዝ ውስጥ ጥይቱ እንደሚገባ በአይምሮየ ‹ካልኩሌት› አደረኩት ....‹‹የአሌክስ አብርሃም የጭንቀት ቴረም››
(ኩላሊት ስኪዌር ...ሲካፈል ለክላሽ ስኪዌር.... ሲባዛ መሳሪያወቹ ለሚያመልጣቸው ጥይት ብዛት ....ሳይንሳዊ ሃቁ ሞት ነው !! )

እኔ በዚህ እሳት ውስጥ ተጥጀ እየፃፍኩ ገጣሚ ጓደኞቸ...ማኪያቶ ፉት እያሉ በሰላሙ አገር ተቀምጠው ‹‹ግጥምህ እምቅነት ያንሰዋል ....እንደውም ግጥም ነው ባትለን ኑሮ ስድ ንባብ ይመስለን ነበር ……ይላሉ …መታመቅን መጥተው ባዩልኝ ! የፍርሃት ላብ ያጠመቀኝ ወዳጆቸ የሰጡኝን ‹ኮሜንት› ሳይ ነው ....በቃ መሞቴን አውቀው ከሰማይ የጠሩኝ አይነት .....

‹‹ብዙነሽ በቀለ›› በሚል የፌስ ቡክ ስም ‹‹...አሌክስየ ፎቶህ ያምራል...በአካል ባይህ ደስ ይለኛል›› የሚል አስተያየት ልካለች አንዷ በዚህ ሰአት እንዲህ ይባላል ......
ጥላሁን ገሰሰ ....መቸ ነው ወደኛ ግቢ(ዩኒቨርስቲ) ብቅ የምትለው አሌክስ
ክቡር ጠ/ሚንስተር መለስ ...ስለመስኖ ስለመንገድ እና ስለግድብ ለምን አትፅፍም...... ከፈለክ ናና አስጎበኝሃለሁ አሌክስ ›› ....
ስብሃት ገ/እግዚያብሄር ....‹‹ አሪፍ ትሞክራለህ ...ጭብጨባ እንዳያጠፋህ አሌክስ ! አንድ ቀን...ያውም በቅርቡ ተገናኝተን እናወራለን እስቲ በርታ እስክንገናኝ!!››እንግዲህ በእነዚህ በተከበሩ ሰወች ስም እራሳቸውን የሰየሙ ሰወች በተከታታይ አስተያየት ሲልኩልኝ ያውም ሞት አፋፍ ላይ ቁሜ እነዴት ነው የማልፈራው .....

ቀስ ብየ ወደአንዱ ፌዴራል ፖሊስ ጆሮየን ጣልኩ ...‹‹ አገሩ ተመቸሽ ....›› ይላል አረብ አገር የሄደች ወዳጁ ጋር ነው የሚያወራው ...ሌላኛው ‹‹ ሰላም ነን እኛ ...እናንተ እንዴት ናችሁ እመየስ ተሸላት›› ይላል ክፍለ ሃገር ቤተሰቦቹ ጋር እያወራ ነው ....ሴቷ ፌዴራል ፖሊስ ‹‹የኔ ጌታ አንተ እማ እንኳን በምንግስትና በአማፂያን መካከል በእግዜርና በሰይጣን መካከል ብትመደብ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንደምታስጠብቅ አምንበሃለሁ ...ናፍቀኸኛል ግን .....በናትህ አንዷ ቆንጆ ልብህን እንዳታሸፍትብኝ..... ››ትላለች ኸረ ፍቅር ....!! ጥቁሩ ፌዴራል ፖሊስ አሁንም ይዝታል ....‹‹ግዴለም ....የሰው ጀግና የለውም የጊዜ እንጅ ....አሳይሻለሁ ...›› እያለ .....
በኋላ እንደተረዳሁት ኢንተርኔቱ ቤት ጎን የፌዴራል ፖሊስ ካምፕ ነበር ለካ!! ከዛ ነው ብቅ እያሉ በየአገሩ ያሉ ወዳጆቻቸው ጋር የሚጨዋወቱት ...የሚፎክሩት እና እንደኔ አይነቱን ልብ የሚያሸብሩት .......ሂሳቤን ከፍየ ውልቅ ስል ግጥሜን እያምሰለሰልኩ ነበር

ገንፎ ....
ስላንች ለመፃፍ አንዲት ላፕቶፕ ባጣ
አፈሙዝ መካከል ሁኘ ነበር ቋንጣ ...መንገዴን ቀጠልኩ ወደኋላ ዞር እያልኩ ማየት ሳረሳ (ወንድ ልጅ የሚከተለው አይታወቅም ሂሂ ፈራን በዲፕሎማሲ ቋንቋ! )