"እስሩ የመንገዳችን አንዱ ተግዳሮት ነው!" - የዞን 9 ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ

ከ15 ደቂቃ በፊት ከጋዜጠኛና ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ጋር አሁን ታስሮ በሚገኝበት በየካ ክ/ከተማ የመሪና አከባቢው የማህበረሰብ አገልግሎት ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ለ 20 ደቂቃዎች ያህል መነጋገር ችዬ ነበር።

በፍቄ በፖሊሶች ተጠርቶ እንደመጣ ሲያየኝ ፈገግ አለ። "አንተ አሸባሪ እንዴት ነህ?" አልኩት። እየሳቀ ሰላም መሆኑን ገለጸልኝ። በመካከላችን አንስተኛ ጠረጴዛ ብቻ ብትኖርም እጅ ለእጅ መጨባበጥ ግን እንደማይቻል ነገረኝ።

...ስለእስሩ ጉዳይ ነገረኝ። "ኮማንድ ፖስቱን (በቪኦኤ) ማጥላላት ..." የሚል የፖሊስ ክስ እንደቀረበበትና ለዚህም የሚያምንበትን ቃል ለፖሊስ መስጠቱን አወጋኝ። 
ከቃለ ምልልሱ ጋርም በተገናኘ አንዳንድ እዚህ ላይ የማይጻፉ ነገሮችንም ጠቆም አደረገኝ - በግርምት ፈገግ እያለ። 
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ታስሮ መፈራቱን የሚገልጽ ነገር በፖሊስ ክስ ላይ እንደተጻፈበት አስረዳኝ።

"እዚህ ይዘውኝ የመጡት ባሳለፍነው አርብ ማታ ሰለነበረ፣ በትክክክል የት አከባቢ እንደታሰርኩአላውቀውም" ሲልም ጠይቆኝ ነበር - በፍቄ። ፖሊስ ጣቢያው ከሲ ኤም ሲ አደባባይ በታች በደርግ ጊዜ ከተሰሩት መኖሪያ ቤቶች (አልታድ) ፊት ለፊት መሆኑን ነገርኩት። እኔም ይህንን ፖሊስ ጣቢያ ያወኩት አቤል ዋበላ (ጦማሪ) በምልክት ነገሮኝ ነው።

በፍቄ ከአራት ጦማሪ ጓደኞቹ ጋር ከዚህ ቀደም በተከሰሱበት ጉዳይ አቃቤ ህግ ይግባኝ በጠየቀባቸው መሰረት፤ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የፊታችን ማክሰኞ ዕለት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ጉዳይ ላይ ከበፍቄ ጋር ትንሽ አውርተን ነበር። አሁን ላለበት ፖሊስ ጣቢያ መጥሪያ ካልተጻፈ በፍርድ ቤት ቀጠሮ ቀን ላያቀርቡት ስለሚችሉ ነገ ማመልከቻ እንደሚያስገባና ጠበቃ አምሃ መኮንንም ዛሬ መጥቶ እንዳነጋገረው በፍቄ ይናገራል።

...ያው ከበፍቄ ጋር የመሰነባበቻችን ሰዓት ሲደርስ "እኔ ሰላም ነኝ። እስሩ በመንገዳችን ላይ ያለ ተግዳሮት ነው" ብሎኛል። በፊቱ ላይ ነጻ የመሆን ፈገግታና ጥንካሬን አንብቤበታለሁ።

እንግዲህ የዛሬዋ ኢትዮጵያችን አንድም ይህቺን ትመስላለች።
ይኽው ነው።

ከኤልያስ ገብሩ ጎዳና